ጥምረቱ በቅርቡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን ያልተገባ አስተያየት ተቃወመ

መጋቢት 15/2015 (ዋልታ) 13 ተቋማትን የያዘው ዓለም አቀፍ የትብብር ጥምረት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በቅርቡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን ያልተገባ አስተያየት በመቃወም መግለጫ አወጣ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንና የውሀ ሀብት ፕሮጀክቶች አስተዳደርን ለመደገፍ የተቋቋመው ጥምረቱ በቅርቡ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ሙሌት መቃረቡን ተከትሎ ‘ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው’ በማለት የሰጡትን ያልተገባ አስተያየት ተቃውሟል፡፡

ጥምረቱ በመግለጫው የግብጽ መንግስት ተመሳሳይ የጦርነት ፍላጎትን የሚያንጸባርቁ ዛቻዎችን በላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ በማቅረብ እንደሚታወቁ አስታውሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የሰጡት ያልተገባ አስተያየትም ከተለመደውና ምክንያታዊነት ከሚጎድለው የመንግስታቸው አካሄድ ያልተለየ መሆኑን አስገንዝቧል።

ጥምረቱ አክሎም የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግብጽ ምንም አስተዋጽኦ የማታበረክትበትን ውሀ በበላይነት ለመቆጣጠር የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆምና በህግ እንድትገዛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሶ በግብጽ በኩል ራሷን እንደ አንድ የተፋሰሱ ሀገርና የእኩል መብቶች ተጋሪ የማየት ችግር አለ ብሏል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታና ሙሌት ጎን ለጎን ማካሄድ እንደምትችል ያስታወሰው መግለጫው በዚሁ ስምምነት መሰረት ሦስት ጊዜ በተካሄደው ሙሌት ምንም አይነት ጉዳት በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ አልተፈጠረም ብሏል።

አራተኛው ሙሌት በዕቅዱ መሰረት እንዳይካሄድ ለማስተጓጎልና የዓለም ውሀ ፎረም ተሳታፊዎችን ለማሳሳት በማሰብ ሚኒስትሩ አስተያየቱን መስጠታቸው የግብጽ መንግስትን ቀቢጸ ተስፋ እንቅስቃሴ የሚያሳይ እርምጃ ነው ማለቱን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ጥምረቱ በመጨረሻም የግብጽ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ አለኝ ብሎ የሚያስበውን የበላይነት ስሜት በመተው ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራና የአባይ ውሀ አሁን ባለውም ሆነ በቀጣዩ ትውልድ በፍትሐዊነት፣ በምክንያታዊነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት አሳስቧል።