ከቆጣሪ ውጭ ኤሌክትሪክ በመጠቀም እንጀራን ከባዕድ ነገር በመቀላቀል ጋግረው ሲያከፋፍሉ የነበሩ ህገ ወጦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 13 የማኅበር ቤቶች ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ እንጀራን ከባዕድ ነገር ቀላቅለው በመጋገር ሲያከፋፍሉ የነበሩ ህገ ወጦች በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ቤቱ ለእንጀራ ማምረቻ መስፈርት የማያሟላ እንደሆነ የወረዳ 13 የምግብ እና መጠጥ ብቃት ማረጋገጥ ቡድን መሪ አዳነ ከበደ ተናግረዋል።
በቤቱ ውስጥ ሰጋቱራን ጨምሮ ሌሎች ባዕድ ነገሮች የተገኙ ሲሆን 8 በርሜል የተከለሰ ሊጥ እንዲወገድ በማድረግ ቁሳቁሱ በኤግዚቢትነት መያዛቸው ተገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ ከቆጣሪ ውጭ ኤሌክትሪክ በመቀጠል ኃይል እየተጠቀሙ እንደነበር በመረጋገጡ ግለሰቦቹ ላይ ክስ መመስረቱንም ቡድን መሪው ተናግረዋል።
ግለሰቦቹ የንግድ ፈቃድ፣ የብቃት ማረጋገጫ፣ የአምራቾች የጤና ምርመራ እንዲሁም የግብር ማሳወቂያ ሰነድ እንደሌላቸው አረጋግጠናል ያሉት አቶ አዳነ በአዋጅ ቁጥር 11/2012 መሰረት እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የምግብና መጠጥ ተቋማት ቁጥጥር ቡድን መሪ አለማየሁ ሻውል በባዕድ ነገር የተከለሰው ሊጥ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ለካንሰር እስከማጋለጥ የደረሰ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ በተለይ ያልተጠናቀቁ ክፍት ቤቶች አካባቢ ተመሳሳይ ሕገ ወጥ ተግባር ሊኖር እንደሚችል በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከክፍለከተማው ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።