የካቲት 28/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 201 ቤቶችን ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስረከበ።
ቤቶቹ ከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መሰረት በጥናት ተለይተው በህገወጥ መንገድ የተያዙ ናቸው ተብሏል።
201 የሚሆኑት ቤቶች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለልማት ተነሺዎች ተለይተው የተሰጡ ናቸው።
በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥና ህገወጥን ለመታገል የምሰራው ስራ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ እያንዳንዱ ዜጋ ህገወጥን በመታገል ለከተማዋ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ይታያል ደጀኔ በበኩላቸው፣ በከተማ አስተዳደሩ በተሰራው ጥናት መሰረት ክፍለ ከተማው ባደረገው አሰሳ ህገወጥ ቤቶችን አስለቅቀን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ላለባቸው እንዲሰጥ አድርገናል ብለዋል።
በቀጣይም ህገወጥ ቤቶች እየተለዩ ለአቅመ ደካሞች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ህገ-ወጥ ቤቶቹ እንዲለቀቁ የከተማውን አስተዳደር መመሪያ በመተግበር የተለያዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የተለያዩ ጽህፈት ቤቶች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
(በሱራፌል መንግስቴ)