የካቲት 20/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ የተለያዩ አልባሳትን እና የምግብ ቁሳቁስን ያካተተ ነው።
ከተለያዩ የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የተሰበሰቡትን ቁሳቁስ ከንቲባ አዳነች አበቤ ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን አስረክበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንዱ ሲቸገር መድረስ እንደ ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ እስካሁን በ500 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ለአፋር ክልል ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ባለፉት ዓመታት በክልሉ ለደረሱት በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች የአዲስ አበባ ከተማ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው አሸባሪው የሕወሓት ተላላኪዎች ችግር ለደረሰባቸው የክልሉ ዜጎች ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
በዛሬው እለት በ57 ሚሊየን ብር የሚገመት የአልባሳት እና የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን ድጋፉም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ እና ከሜድሮክ ኢትዮጵያ የተገኘ ነው ተብሏል።
በቁምነገር አሕመድ