መጋቢት 19/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ90 ቀን 108 ቤቶችን ገንብቶ ለአቅመ ደካሞች ለማስረከብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ግንባታ አስጀመረ።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በክፍለ ክተማ የሚገነባውን 108 ቤቶችን የሚይዝ ባለአምስት ወለል ሦስት የመኖሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ነው ዛሬ ግንባታውን ያስጀመሩት።
ከተማ አስተዳደሩ በከተማው ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡን በማህበር በማደራጀት የቤት መስሪያ ቦታ ከመስጠት ጎን ለጎን የአቅመ ደካሞችን የቤት ችግር ለማቃለል እየሰራ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ መኖሪያ ቤት ለሌላቸውና ተከራይተው መኖር ለማይችሉ አቅመ ደካሞች ቤት ገንብቶ ለማስረከብ ግንባታውን አስጀምሯል ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የህዝቡን ተስፋ ለማለምለም፣ በኑሮ ውድነትና በቤት እጦት የሚሰቃየውን ህዝብ በምንችለው ለማገዝ ጥረት እያደረግን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤት በህብረተሰብ ተሳትፎ እና ባለሃብቶች የሚገነባ መሆኑም ተገልጿል።
በግዛቸው ግርማዬ