የኔትዎርኩ መመሥረት የሴቶች የፋይናንስ አካታችነትን ከግብ ለማድረስ አስቻይ ሁኔታ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 19/2016(አዲስ ዋልታ) የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ(ኒውፊን) መመሰረት ሴቶችን የፋይናንስ አካታችነት ከግብ ለማድረስ አስቻይ ሁኔታ ስለመሆኑ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በዓለም ባንክ ትብብር ዛሬ የተመሰረተው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ የፋይናንስ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ያግዛልም ተብሏል።

በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ሂደት ሴቶች የራሳቸው ድርሻ እንዲያበረክቱ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑም ተነስቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ በፋይናንስ አካታችነት መርሐ-ግብር በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለው የተሳትፎና የተጠቃሚነት ድርሻ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ጠቁመው ስትራቴጂው በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት የማጥበብ ዓላማን የሰነቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘላቂነትና መተማመን ያለበት የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት በባንኩ አካታች የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በፋይናንስ ተቋማት ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻል መሆኑን አንስተዋል።

የኔትወርኩ ዓላማ ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ የሚያበቃና የፆታ እኩልነትን የሚያሰፍን የፋይናንስ ዘርፍ ማጎልበት እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።