በሁከት እና ትርምስ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ ሙከራ ጉም እንደመጨበጥ ነው – የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ግንቦት 6/2015 (ዋልታ) በሁከት እና ትርምስ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ ሙከራ ጉም እንደመጨበጥ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ አስታወቀ።

አገልግሎቱ የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ከገባች አምስት አመታት ተቆጥረዋል። በዚህ የለውጥ ዓመታት ይሆናሉ ተብሎ ያልታሰቡ በርካታ ድሎች ተመዝግበዋል። በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ዘርፎች አገራችንን ወደፊት ሊያስፈነጥሩ የሚችሉ በአለት ላይ የተገነቡ መሰረቶች ተጥሏል። ሆኖም ግን የተገኙ ስኬቶች አልጋ በአልጋ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አልተመዘገቡም። ይልቁንም በበርካታ ፈተናዎችን በመሻገር የተገኙ ውጤቶች ናቸው።

ለውጡ ገና ከመነሻው እንዲጨናገፍ መጠነ ሰፊ ሴራዎች ተሸርበው፣ ለውጡን ለማጠልሸትና የለውጥ አመራሩን ተስፋ ለማስቆረጥ ጥቃቶች ተሰንዝሯል፤ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ተከፍቷል። የብርቅዬ አመራሮች እና ዜጎች ህይወት ተቀጥፈዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ጦርነት ተከፍቶ የበርካቶችን ህይወት በልቷል። በአጠቃላይ ሀገርና ሕዝብን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። የእነዚህ ጥፋቶች መነሻቸው በአንድም በሌላም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድና በንግግር ከመፍታት ይልቅ የአንድን ቡድን ጠባብ ፍላጎት በሌላው ላይ በኃይል ለመጫን ከመፈለግ የሚመነጭ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገራችን በዓይነቱና በዲሞክራሲያዊነቱ ልዩ በሆነው ምርጫ ይሆነኛል ያለውን ፓርቲ በመምረጥ ሕገ-መንግሥታዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲመሰረት አድርጓል። በመሆኑም ጉልበትና ትርምስ ከእንግዲህ ወዲህ ለስልጣን እንደማያበቁና ጠብመንጃ የመንግሥት ስልጣን ምንጭ የሚሆንበት ምዕራፍ እንዲዘጋ ሆኗል።

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ልምምድ ሂደት ውስጥ በመግባቷ በሃሳብ ብልጫና በምርጫ ለማሸነፍ ያልቻሉና ተስፋ የቆረጡ ቡድኖች በብሄርና በሰፈር ማንነት እየማሉ ጽንፈኛ አስተሳሰብን በማቀንቀን መንግሥትን በኃይል ለማንበርከክ ያልቆፈሩት ጉድጓድና ያልተጓደኙት ኃይል የለም። በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በፅንፈኝነት አስተሳሰብ የተደራጁ ቡድኖች የሕዝብን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል።

እነዚህ እኩይ ኃይሎች በሆነ ጊዜ በብሔር መብት አስጠባቂነት፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ በኃይማኖት መብት አስካባሪነት ስም ቢንቀሳቀሱም፤ ዓላማቸው በሃሳብ ተወዳድሮ ሊጨብጡ ያልቻሉትን የመንግሥት ስልጣን በኃይል መቆጣጠር ነው።

የእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ ስልት አድርጎ የቀየሱት መንገድ ደግሞ አንድን ብሔር ተበዳይ፣ ሌለውን በዳይ አድርጎ በመሳልና በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን፣ ግጭትና ያለመተማመንን ስሜትን በመፍጠር የጋራ እሴቶቻችንን በመሸርሸር ነው። አካሄዳቸውም በተግባር ከሚፈፅሙት አስነዋሪ ድርጊት ባሻገር እጅግ አሳፋሪና ለኢትዮጵያዊያን ባህል፣ እሴትና ስነ-ምግባር የማይመጥን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ተስተውሏል።

እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች ከራሳቸው ጥቅምና የስልጣን ጥማት ውጪ የማንም ብሔር ሆነ ኃይማኖት ወኪል አይደሉም። አንዱን ቅዱስ ሌላውን አርዮስ በማድረግ፤ ንፁሀንን እየጨፈጨፉ፤ የመንግሥት ኃላፊዎችን እየገደሉ፤ የቁርጥ ቀን ዋስትናችን፣ የሕዝብ መከታ በሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት እየፈጸሙ እና የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት እንዳይኖር እየሠሩ ያሉት እነዚህ አካላት የየትኛውም ብሔር ወኪል ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም ሕገወጥ ድርጊት እየፈጸሙ በብሔሮች ጉያ ውስጥ ለመደበቅ የሚሞክሩትን ፅንፈኞች ሕዝባችን ሊታገላቸው ይገባል። የትኛውም አይነት ጥያቄና ፍላጎት ከወንድማማችነት፣ አብሮነትና እኩልነት ውጭ ሊሳካ እንደማይችል ሁሉም መገንዘብ ይኖርበታል።

መንግሥት ከየትኛውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊና ሕብረብሔራዊ ፌደራሊዝምን ተግባራዊ በማድረግ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሓዊነትና እኩልነት እንዲረጋገጥ በተግባር እያረጋገጠ ባለበት ሁኔታ በኃይልና በጉልበት የራስን እኩይ ፍላጎት በሌሎች ላይ በመጫን የትኛውንም አይነት ፍላጎትም ሆነ ጥቅም ማረጋገጥ እንዳማይቻል ሊገነዘበው ይገባል።

መንግሥትም የፀጥታ መዋቀሮችን በማጠናከር፣ አንድ ጠንካራ መከላከያ ወራዊትን በመገንባት በሀገሪቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል። የክልሎችን የፀጥታ አካላት መልሶ በማደራጀት አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ሰራዊት በመገንባት የመላ ህዝባችንን ደህንነትና ሰላም ለማረጋገጥ የጀመረውን ስራም አጠናክሮ ቀጥሏል።

የትኛውንም አይነት ጥያቄ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል በተለያየ ምክንያት ጠመንጀ አንግቦ ለሚንቀሳቀሱ አካላት መንግሥት ያቀረበው ሰላማዊ አማራጭ አዎንታዊና የተሳኩ ውጤቶች እየተገኙበት ነው። ከዚህ አንፃር በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላም ስምምነት ከመቋጨትም ባለፈ በጋምቤላ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በሌሎችም ክልሎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር የሽምቅ ውጊያ ሲያደርጉ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎችንም ወደ ሰላማዊ ጎዳና በመመለስ የተሀድሶ ፕሮግራም እያከናወነ ይገኛል።

አሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በሀሳብ ልዕልና ተወዳድሮ እና ሀሳብን ለመራጩ ሕዝብ አቅርቦ ማሸነፍ እየተቻለ በአፈሙዝ ሥልጣንን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ለክፍለዘመኑ የማይመጥን እንዲሁም ተሞክሮ የከሸፈ በመሆኑ፣ ከሀሳብ ልዕልና ውጭ ወደ ሥልጣን መምጣት እንዳማይቻል መገንዘብ ይገባል። የሀገራችንን ሰላም እና ፀጥታ በማናጋት የሚሳካ የፖለቲካ ግብ ከእንግዲህ እንደማይኖር መታወቅ ይኖርበታል። አካሄዱም መጨረሻውም ኪሳራ ብቻ መሆኑን ከራሳችን ያለፉ ተሞክሮዎች መማርና መገንዘብ ያስፈልጋል።

መንግሥት በሀገራችን መንፈስ የጀመረው የሰላም አየር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካለው ፅኑ አቋም አንፃር ፅንፈኛ ኃይሎች የሚወስዱዋቸውን እርምጃዎች በትዕግስት ሲያልፍ ቆይቷል። ነገር ግን ፅንፈኛ ኃይሎች መንግሥት የሚያሳየውን ትዕግስት እንደፍርሀት በመቁጠር ዛሬም በጥፋታቸው ቀጥለውበታል። መንግሥት በተደጋጋሚ እንደገለጸው ለየትኛውም የሃሳብ ልዩነት ጠብመንጃ ማንሳት ሳይሆን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ቅድሚያ የሚሰጥ ቢሆንም የሕዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ ግን ሕግ የማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ ይቀጥላል። ሕዝባችንም የፅንፈኞችን ሀገር አፍራሽ ተግባር በመገንዘብ እንደተለመደው ከመንግሥት ጎን በመቆም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚጠበቅበትን ሁሉ እዲወጣ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።

ግንቦት 6/2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት