ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት የለም – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ሚያዝያ 7/2015 (ዋልታ) ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት የሌለ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌዴራልና የክልል የጸጥታ ተቋማት መልሶ የማደራጀት ስራ የመከላከያ ጀነራሎች፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የክልል ልዩ ኃይሎች እንደገና በመደራጀታቸው ህብረ ብሄራዊ ጠንካራ የጸጥታ ተቋም ይገነባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከነበረችበት የጸጥታ ችግር በፍጥነት መውጣቷን የገለጹት ፊልድ ማርሻሉ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት ህጋዊ አለመሆን፣ በክልሎች መካከል እንደ ስጋት መተያየት እንዲሁም ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ አደረጃጀቱን ለመቀየር አስገድዷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች መልሶ የማደራጀት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው “ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀትና መዋቅር የለም” ሲሉም አክለዋል።

በመሆኑም የጸጥታ መዋቅሩ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ሲሆን በክልል ልዩ ኃይሎች ስም ተልዕኮም ሆነ ግዳጅ የሚቀበል ኃይል አይኖርም ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በኋላ በመረጡት አደረጃጀት መሰረት ሁሉንም ወደ ተመደቡበት የማጓጓዝና ወደ ስልጠና የማስገባት ስራ ይከናወናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።