ከድሬድዋ ወደ ጅግጅጋ ሲጓዝ የነበረ ET-AMl የተሰኘ  አውሮፕላን ተከሰከሰ

ሐምሌ 21 ፣ 2013 ( ዋልታ) አራት ሰዎችን አሳፍሮ ከድሬድዋ ወደ ጅግጅጋ ሲጓዝ የነበረ ET-AMl የተሰኘ  መለስተኛ አውሮፕላን በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ  ተከሰከሰ፡፡

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁለቱ አብራሪዎች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰራተኞቸ መሆናቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ከሚገኘው መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ንብረት የሆነችው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት ሰዎች የደረሰባቸው ጉዳት ለህይወት አስጊ እንዳልሆናና በድሬደዋ ከተማ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አውሮፕላኑ ትላለንት ከቀኑ 11:30 አካባቢ በኮምቦልቻ ወረዳ ቄረንሳ ጋረአሮ በተባለ ቦታ መውደቁን የወረዳው ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

አውሮፕላኗ በድርጅት የበረራ ደንበኛ አብሲኒያ የበረራ አገልግሎት ሲበር እንደነበረም ከወጣው መግላጫ ታውቋል፡፡

የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ ለማወቅ በኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን፣አብሲኒያ የበረራ አገልግሎት እና በዓለም ምግብ ፕሮግራም እየተጣራ መሆኑም ተገልጿል፡፡