ከ106 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኮንትሮባንድ እቃዎች

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) ባሳለፍነው ሳምንት 106 ሚሊዮን 170 ሺሕ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽ አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል 92.8 ሚሊዮን ብር  የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 13.3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዙን ጠቁሟል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ድሬዳዋ፣ አቃቂ ቃሊቲ እና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 25.4 ሚሊዮን፣ 16 ሚሊዮን እና 15.6  ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል ነው የተባለው፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ የበት ክዳን ቆርቆሮ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች እንደሚገኙ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኮሚሽኑ በህግ ማስከበር ሥራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ኅብረተሰቡን አመስግኗል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ኮሚሽኑ ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡