ግብፅና ሱዳን የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መደገፍ አለባቸው – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

    አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብ ግንባታን በፍጥነት እንድታጠናቅቅ ግብፅ ማበረታታት አለባት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከአል-አረቢያ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የግድቡ መገንባት ግብፅን በድርቅ ወቅት እንኳ የውሃ ቋት ሆኖ  የሚያገለግል ፕሮጀክት በመሆኑ ፕሮጀክቱን ልትደግፈው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሱዳን በአነስተኛ ግድቦቿ ላይ ይደርስብኛል ብላ የምታነሳውን የደኅንነት ስጋት በሚመለከት  መደበኛ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች አቋሟን አስርድታለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሀገሪቱ ግን አሁን ላይ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የሶስተኛ ወገን ጉዳይ አስፈፃሚ አየሆነች መምጣቷን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ አንድ ወገን ብቻ ከዓባይ ሀብት ተጠቃሚ ሲሆን ዘላለም አለሟን መጠበቅ አትችልም ያሉት አምባሳደር ሬድዋን በመሆኑም ሱዳን እና ግብፅ አሁን ከያዙት ግትር አቋም መላቀቅ አለባቸው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ተቀመጫነቱን ዱባይ ካደረገው የአል-አረቢያ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በሚመለከት ብዙ አዎንታዊ የሆኑ እድሎችን አቅርባ እንደነበር ገልጸው ግብፅና ሱዳን ባለመቀበላቸው ምክንያት ሳይሳኩ እንደቀሩ ጠቁመዋል።

የኅዳሴ ግድብ ከጭቅጭቅ ይልቅ የቀጣናዊ ኅብረትና አንድነት ማሳያ እንደሆነና ኢትዮጵያ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት የጎላ ጉዳት ሳታደረስ የራሷን ሀብት መጠቀም እንደምትችል ገልጸዋል።

የሱዳንን አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ በሚመለከት ሁሉም ወገኖች ከምንም በላይ ሀገራቸውን ማስቀደምና የሱዳናዊያንን ጥቅም ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሁሉም ፓርቲዎች የሀገሪቱን ዜጎች ጥቅም ከሁሉ ነገር በላይ በማስቀደም ነገሮችን በእርጋታና ምክንያታዊነት የሚያስኬዱ ከሆነ ልዩነቶቻቸውን ማስታረቅ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል የታየ ተነሳሽነት ካለ በሚል ከጋዜጠኛዋ ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ሬድዋን የሱዳን ሕዝብ ችግሮቹን ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የመፍታት ጥበብ እንዳለው አስረድተዋል።

ለኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን ለመቋጨት ወታደራዊ ኃይል በምንም መልኩ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣና አስፈላጊው ነገር ኢትዮጵያ እንዳደረገችው የተሻለ የመፍትሄ ሀሳብ ወደ ጠረጴዛ ይዞ መቅረብ ነው ብለዋል።

ወደ ትግራይ ክልል የሚቀርብ የእርዳታ ድጋፍን በሚመለከትም ምንም እንኳን ታጣቂ ቡድኑ የሰብኣዊ ድጋፍ በተገቢ መልኩ እንዳይቀርብ እንቅፋት እየሆነ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከሰብኣዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያልተገደበ ድጋፍ በክልሉ እንዲደረግ የሚችለውን ሁሉ እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ባለው ግጭት የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሚመለከትም በርካቶች ኢትዮጵያን የማዳከም ፍላጎት እንዳላቸው መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።

አብዛኞቹ ጣልቃ ገብነቶችም መንግሥት ያከናወናቸውን መልካም ሥራዎች ላለማበረታታትና ዝቅ ለማድረግ እንደሆነ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡