ከ19 ሺህ በላይ ጥይቶችን ወደ ባህር ዳር ሊያስገቡ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – 19 ሺህ 739 ተተኳሽ ጥይቶችን በባለሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህር ዳር ሊያስገቡ የሞከሩ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በጉምሩክ ኮሚሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አለነ መሀሪ ግለሰቦቹ የቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ጥይቶቹን ከምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ከደለጎ ከተማ ወደ ባህር ዳር ለማስገባት ሲሞክሩ ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-43622 አ.ማ በሆነ በባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህርዳር ለማስገባት ሲሞክሩ በሻውራ ጉምሩክ ሰራተኞችና በፌደራል ፖሊስ ትብብር በተደረገ የኬላ ፍተሻ መያዛቸውን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ለፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተው ጉዳዩ እንዲጣራ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የማህበረሰቡንም ሆነ የሃገሪቱን ሰላም የሚጎዳ በመሆኑ ህብረተሰቡ መሰል ወንጀሎች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ስራ አስኪያጁ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።