ከ195 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኮንትሮባንድ እቃዎች

የካቲት 25/2015 (ዋልታ) ከ195 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከየካቲት 17 ቀን እስከ 23/2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 129 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 66 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የወጪ በድምሩ ከ195 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን አመልክቷል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ ሀዋሳ፣ አዋሽ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 23 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ 19 ነጥብ 2 ሚሊዮን እና 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻላቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ዘጠኝ ግለሰቦች እና ዘጠኝ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ በህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ህዝቦች ምስጋናውን በማቅረብ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡