ከ350 ሄክታር በላይ የበልግ ስንዴ ማምረት መቻሉን ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ

ግንቦት 01/2013 (ዋልታ) – በዚህ ዓመት ከ300 ሄክታር በላይ የበልግ ስንዴ ለማምረት ታቅዶ ከ350 ሄክታር በላይ ማምረት መቻሉን ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ትላንትና የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የግብርናው ዘርፍ ማዘመን ካልተቻለ የአርሶ አደሩ ህይወትም ሆነ ኢትዮጵያም እንደሀገር አትቀየርም ያሉ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለውን የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር ይሰራል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ሰላም በማስጠበቅና ወንድማማችነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና እውን ማድረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን እና 6.5 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብን ታላሚ ያደረገ ነውም ተብሏል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ፓርኩ ለአምራች አርሶ አደሮችም ሆነ ለሀገር የሚጠቅም ከመሆኑም በላይ የግብርናው ዘርፍ እንዲዘምንና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማት የተሟላለት ሲሆን የአስተዳደር ህንፃ ፣ የህክምና ስልጠና እና የመዝናኛ ማዕከላትን አካቷል ያሉት ደግሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል ናቸው።
የቡልቡላ ኢንደስትሪያል ፓርክ በተለይም የሥጋ ውጤቶች፣ የፍራፍሬ እና አትክልት፣ ቡና፣ እንቁላል እንዲሁም እህል የሚቀነባበሩበት ሲሆን አጠቃላይ የግንባታው ወጪም እስከ 9 ቢሊየን ብር እንደሚደርስ ተገልጿል።
(በደረሰ አማረ )