ካሰብነው የእድገት ማማ ለመድረስ የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል – ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ግንቦት 05/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያን ካሰበችው የእድገት ማማ ለማድረስ የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር እና መሰናክሎችን በመበጣጠስ መሻገር ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በ1ሺህ 442ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ሀገራችንን ለማፈራረስ ሌተ ቀን የሚታትሩ ሀይሎች በብሔርና በሐይማኖት ለመነጣጠል ስውር አላማቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ሙከራ ፈፅሞ እንደማይሳካ ገልፀዋል፡፡
የዘንድሮው በዓል ክብረ ወሰንን የሰበረ እና ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እንድትወጣ ዱአ በማድረግ ሙስሊሙ ማህበረሰብ አርአያነት ያለው ተግባር በመፈፀም ያሳለፈው የፆም ወር ነበር ብለዋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ አያይዘውም የዘንድሮው የረመዳን ወር በመዲናችን አዲስ አበባ ከሌሎች የሀይማኖት ተከታዮች ጋር በጋራ ሆኖ በማፍጠር አንድነትን በማሳየት የአብሮነት እሴቶቻችን ላይ እያንዣበበ የመጣውን አቧራ ለማራገፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
የረመዳን ወር በፆም በፀሎት፣ በይቅርታ፣ በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ የምናከብረው ለአንድ ወር ብቻ ረመዳንን ጠብቀን የምናደርገው ሳይሆን ሁልጊዜ መቀጠል ያለበት መልካምነት ነው ሲሉ ወ/ሮ አዳነች አክለዋል፡፡
(በአመለወርቅ መኳንንት)