ኮሌጆች የቀድሞ ታጣቂዎች በመልሶ ግንባታ ስራ እንዲሰማሩ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል – ጀነራል ታደሰ ወረደ

ሐምሌ 30/2015 (ዋልታ) የቀድሞ ታጣቂዎች ሙያዊ ክህሎት ተላብሰው በመልሶ ግንባታ ስራ እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ኮሌጆች ድርሻ የጎላ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጀነራል ታደሰ ወረደ ገለጹ።

በክልሉ የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ዘርፉን ስራ ለማስጀመር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጀነራል ታደሰ ወረደ እንዳሉት በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ የመንግስትና የግል ሙያና ቴክኒክ ስልጠና ኮሌጆች ፈጥነው ወደ ስራ ሊገቡ ይገባል።

ኮሌጆቹ ወጣቶች ሙያዊ ክህሎት በመላበስ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይም ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለከሱ የቀድሞ ታጣቂዎች ሙያዊ ክህሎት ተላብሰው በሙሉ አቅማቸው በመልሶ ግንባታ ስራ እንዲሳተፉ የማድረግ የጎላ ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ሲገቡ በሙያና ቴክኒክ ሰልጥነው ወደ ስራ እንደሚሰማሩ መንግስት ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል” ብለዋል።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ቢሮ የስራ እድልና ፈጠራ ዳይሬክተር ገነት አረፈ በበኩላቸው ኮሌጆቹ የሚሰጧቸው የሙያ ስልጠናዎች ለውጥ ማምጣት የሚችሉ እንዲሆኑ ባለሀብቶች፣ ዳያስፖራዎችና ባለድርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

እንደኢዜአ ዘገባ የመንግስትና የግል ኮሌጆቹ በመደበኛና በአጭር ስልጠናዎች በየዓመቱ ለ111 ሺሕ ወጣቶች ሙያዊ ስልጠና የመስጠት አቅም ያላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።