ኮሚሽኑ ለምክክሩ ሂደት ትግበራ ሁሉም የኅብረተስብ ክፍሎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለተቋቋመለት ሀገራዊ አጀንዳ ተግባራዊነትና ውጤታማነት ሕዝቡ፣ ሁሉም የኅብረተስብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ፡፡

ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሦስት ወራት ዕድሜ ውስጣዊ የአሰራር ድንጋጌዎችና መመሪያዎች ከማውጣት ባሻገር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትውውቅ ማካሄዱን ለዋልታ በላከው ወቅታዊ መልዕክት አመልክቷል፡፡

ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ለምክክሩ ሂደት ትግበራ ስኬታማነት ወሳኝ በመሆኑ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣  የሰላም እናቶችና ወጣቶች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ከምን ጊዜውም በተጠናከረ ሁኔታ አካባቢያዊና ሀገራዊ እርቅ ለማምጣት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ነው ጥሪውን ያስተላለፈው፡፡

ኮሚሽኑ በመልዕክቱ በየቦታው ያለው ግጭትና ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ሁሉም ወገኖች ወደ ውይይት እንዲመጡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ወኖችንና ሰላም ወዳዱ ዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግም ጠይቋል።