የአፍሪካ ሚዲያዎች የአገርን ጥቅም ማስከበር ላይ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ተባለ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) “የአፍሪካ ሚዲያዎች የአገርን ጥቅም ማስከበር ለሚችሉ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት መስራት ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሀ ይታገሱ ገለጹ።

በቱርክ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በተዘጋጀው የቱርክ አፍሪካ ሚዲያ ጉባኤ ላይ የመወያያ ሀሳብ ያቀረቡት ፍስሀ ለሀገሩ ጥቅም መከበር የማይሰራ የሚዲያ ተቋም እንደሌለ ተናግረዋል።

በመሆኑም የአፍሪካ አገራት ሚዲያዎች ለሀገር ገጽታ ግንባታ እንዲሁም ለሀገር ጥቅም በመቆም የሚዲያ ሥራዎቻቸውን መቃኘት የግድ እንደሚላቸው ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም ብዝኃነት ያላቸው አገራት ብዝኃነታቸውን ጠብቀው ጠንካራ አንድነት እንዲኖራቸው ለማስቻል የሚዲያዎች ሚና የላቀ በመሆኑ በዚህ ረገድ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ባበቃበት ወቅት በኢትዮጵያ ወደስልጣን የመጣውና በአሸባሪው ሕወሓት ይመራ የነበረው ቡድን ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ብዙ ጥፋት ማድረሱን ጠቅሰው ቡድኑ ለህግ የማይገዛና በሙስናና ሌሎች ወንጀሎች ውስጥ የተዘፈቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕወሓት በኢትዮጵያ ጦርነት መለኮሱ እየታወቀ የምዕራባዊያን ሚዲያዎችና ዲፕሎማቶች እውነታውን አዛብተው በመዘገብ የኢትዮጵያን መንግሥት በተደጋጋሚ ሲወነጅሉ መክረማቸውን አብራርተዋል።

“ኢትዮጵያ ላይ ፍትሐዊነት የጎደለው ጫናና ዘመቻ እየተደረገ ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ12 ጊዜ ያላነሰ ስብሰባ መጥራቱን ጠቅሰዋል።