ኮሚሽኑ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ከውጭ ባለሃብቶች ጋር ውይይት እያደረገ ነው

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ባሻገር ለባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ከተለያዩ የውጭ ሀገር ባለሃብቶች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

ኮሚሽኑ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱን ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል ያለው መርኃግብሩ በዛሬው እለት ሲጀመር ከቱርክ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ኤዥያ ባለሃብቶች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶች  እና መልካም ጎኖች ተነስተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ኔሚ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በኢንቨስትመንት ዘርፉ 4ኛ ተመራጭ ሀገር በመሆኗ ጠንክረን መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአለም አቀፍ ደረጃ ባስከተለው የአለም ኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የተጎዳውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ በአዲስ ፓሊሲ በማፅናት ለመስራት መንግስት አዋጅ ማውጣቱን አስታውሰው፣ ይህም ለውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች መልካም እድልን እንደምፈጥር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያዘጋጀው ውይይት፣ በቀጣይ ከህንድ  የመጡ ኢንቨስተሮችን እንዲሁም  የኢንዱስትሪያል ፓርክ ባለሃብቶችን በማካተት  ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ውይይቱን እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።

(ቁምነገር አህመድ)