የአውሮፓ አቪየሽን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ዳግም መብረር እንዲችል ፈቀደ

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን

 

የአውሮፓ የአቪየሽን ደኅንነት ኤጀንሲ (EASA) የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከዚህ በኋላ ወደ በረራ ለመመለስ ዝግጁ ናቸው ሲል አረጋገጠ።

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓትሪክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አውሮፕላኖቹ ከዚህ በኋላ ለመብረር አንዳችም ስጋት እንደሌለባቸው እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን ብለዋል።

ድርጅታቸው ከአውሮፕላኖቹ አምራች ጋር በመሆን ጥብቅ ፍተሻና ምርመራ እንዳደረገና ለበረራ ዝግጁ እንደሆኑም እንዳረጋገጠ አብራርተዋል።

አውሮፕላኖቹ ከበረራ የተገለሉት በአወሮፓውያኑ 2019 እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አውሮፕላኖቹ ከበረራ የታገዱት በኢትዮጵያና በኢንዶኔዢያ ሰማይ ላይ ተከስክሰው 346 መንገደኞች መሞታቸውን ተከትሎ ነው።

አሁን የቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች በአሜሪካ እና በብራዚል፣ ከጥር አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ በመላው አውሮፓ በረራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

የማክስ አውሮፕላኖች የመጀመርያው አደጋ የተመዘገበው በላየን አየር መንገድ ሲሆን፣ ይህም በጥቅምት 2018 በኢንዶኒዢያ ሰማይ ላይ ነበር።

ሁለተኛው አደጋ ደግሞ ወደ ናይሮቢ በማቅናት ላይ በነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ እንደነበር ይታወሳል።

የሁለቱም አደጋዎች ምንጭ ከአውሮፕላኑ የአደጋ ጊዜ ሶፍት ዌር እንከን ጋር የተያያዘ እንደነበር አይዘነጋም።

ሶፍትዌሩ ራሱን በራሱ የሚያዝና፣ በተሳሳተ ጊዜ ራሱን የሚያነቃ ሆኖ የተሰራ ሲሆን፣ አውሮፕላኑን ከአብራሪው ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን የሚያደርግ ሆኖ በመነደፉ እክል እንደነበረበት በኋላ ላይ ተረጋግጧል።

የአውሮፓ አቪየሽን ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊ እንደተናገሩት እነዚህ እክል የነበረባቸው አውሮፕላኖች ወደ ሰማይ እንዲመለሱ ለመወሰን የነበረባቸው እክል ብቻ መመርመር በቂ አልነበረም፤ ስለዚህ መላ ስሪታቸውን እንደ አዲስ ፈትሸን ነው እንዲመለሱ የወሰንነው ብለዋል።

ለማክስ አውሮፕላን የተገጠመለት አዲስ ሶፍትዌርን በተመለከተ አብራሪዎች አዲስ ስልጠና እንዲወስዱ ይገደዳሉ ተብሏል።