ኮሚሽኑ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው አለ

ታኅሣሥ 21/2015 (ዋልታ) በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊየን፣ በአማራ ክልል 2 ነጥብ 4 ሚሊየን እንዲሁም በአፋር ክልል 715 ሺሕ 132 የእለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡

ለዚህም ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም (ዶ/ር) በየብስ አፋር አብዓላ መስመር፣ በጎንደር ሁመራ ሽሬ መስመር፣ በኮምቦልቻ ቆቦ መስመር ድጋፍ እየተጓጓዘ ነው ተብሏል።

በአየር በመቀሌ እና በሽሬ ኤርፖርቶች የእለት ደራሽ ዕርዳታ እየደረሰ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለመጀመሪያ ዙር በትግራይ 88 ሺሕ 179 ሜትሪክ ቶን፣ በአማራ ክልል 41 ሺሕ 371 ሜትሪክ ቶን በአፋር ክልል ደግሞ 12 ሺሕ 121 ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በሁለተኛ ዙር በትግራይ ክልል 24 ሺሕ 960 ሜትሪክ ቶን በአማራ ክልል 1 ሺሕ 887  እንዲሁም በአፋር ክልል 1 ሺሕ 387 ሜትሪክ ቶን እየተሰራጨ ይገኛል ተብሏል።

በብርቱካን መልካሙ