ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገለጸ

ንጉሱ ጥላሁን

መጋቢት 28/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ከተለያዩ የግልና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የፌዴራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ለአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል።

ከዚህ ውስጥ 38 በመቶው ጊዜያዊ የስራ እድል ሲሆን፣ 62 በመቶው ደግሞ ቋሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም በሀገሪቱ አሁን ካለው የስራ አጥ ቁጥር አንጻር ጋር ሲነጻጸር ለስራ ፈጠራ በቀጣይም ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።

የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ በተለይ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።

የስራ እድሎች ላይ የቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚነትን 80 በመቶ ለማድረስ እንደሚሰራ ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ ይህን እውን ለማድረግ ከግልና ከመንግስት ተቋማት፣ ከኢንዱስትሪዎችና ከፋብሪካዎች ጋር የቅንጅት ስራ በስፋት ይከናወናል ብለዋል።

ከሌሎች አገራት ልምድ በመውሰድም አዳዲስ የስራ መስኮችን ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉም አመልክተዋል።

በኮቪድ-19 ሳቢያ በርካታ የስራ እድሎች መምከናቸውን ያስታወሱት አቶ ንጉሱ፣ ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ወደ ስራ ለመቀየር የሚያስችል ዝግጁነት እንደሚያስፈልግና የሚፈጠሩ ስራዎችን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ማጣጣም የሚያስችል አቅምን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በስራ እድል ፈጠራና በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ልምዳቸውን ለወጣቶች የሚያካፍሉበት መድረክ እንደሚያመቻችም ገልጸዋል።

ወጣቶች በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በሚፈጠሩ የስራ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ2 ሚሊየን በላይ አዳዲስ ስራ ፈላጊ ዜጎች ወደ ገበያው የሚቀላቀሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 200 ሺህ የሚሆኑት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።