ኮሚሽኑ ከ151 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን ያዘ

መስከረም 15/2015 (ዋልታ) ከ151 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከመስከረም 6 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 144 ነጥብ 1 ሚሊየን የገቢ እና 7 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ 151 ሚሊየን 287 ሺሕ ብር ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውም ተገልጿል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚዎቹ አዳማ፣ ሞያሌ እና አዋሽ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 34 ነጥብ 5 ሚሊየን፣ 28 ነጥብ 1 ሚሊየን እና 21 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ይዘዋል፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 23 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡