ኮንግረሱ በቲክቶክ ላይ የጣለው እገዳ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅን መብትን የሚሸረሽር ነው ተባለ

ሚያዚያ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) የባትዳንስ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በአሜሪካ ኮንግረስ ትናንት የተጣለበት እገዳ የ170 ሚሊዮን አሜሪካዊያንን ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል አስጠነቀቀ፡፡

አገልግሎቱ እንዲታገድ ባለፈው ቅዳሜ የአሜሪካ የታችኛው ምክር ቤት የሆነው ኮንግረሱ በ360 ድጋፍና በ58 የተቃውሞ ድምፅ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ከአንድ ሳምንት በኋላ ህግ ሆኖ ይጸድቃል ተብሏል።

ኮንገረሱ ኩባንያው ከቻይና መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥና ያለውን ድርሻ ቻይናዊ ላልሆኑ ኩባንያዎች እንዲሸጥ የጠየቀ ሲሆን የመጨረሻው አማራጭ ግን አሜሪካን ውስጥ አገልግሎት ከመስጠት እንዲታገድ የሚል ነው።

ኮንግረሱ ቲክቶክ በወጣት አሜሪካዊያን ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱ እንዳሳሰበውና ኩባንያው የአሜሪካዊያን ተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግስት አሳልፎ ይሰጣል በሚል ፍራቻ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስቻለው።

የዕግድ ውሳኔው ህግ ሆኖ ከጸደቀ ባይትዳንስ ድርሻውን ለመሸጥ የ9 ወራት ጊዜ እንደሚኖረው ነገር ግን ለመሸጥ ፈቃደና ካልሆነ ቲክቶክ በአሜሪካ አገልግሎቱ ይታገዳል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

የቲክቶክ ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ በሰጠው አስተያዬት ውሳኔው የ170 ሚሊዮን አሜሪካዊያን የመናገር ነጻነት ከመጣሱም በላይ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ገቢያቸው ከቲክቶክ ጋር የተያያዘ የንግድ ድርጅቶች ህልውና ሊያበቃ ይችላል ብሏል። ቲክቶክ ለአሜሪካ ኢኮኖሚ በዓመት ከ24 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተጠቅሷል።

በፈረንጆቹ 2012 በቻናዊያን ስራ ፈጣሪዎች የተመሰረተው ባይትዳንስ በ2013 ቲክቶክን ወደ ስራ በማስገባት ታዋቂ እየሆነ መምጣቱና በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይገመታል።

የባይትዳንስ መስራቾች ከፍተኛ የመወሰን መብት የሚያስገኘውን 20 በመቶ ድርሻ የያዙ ሲሆን 60 በመቶው ደግሞ በአሜሪካ ኩባንያዎች የተያዘ ነው። ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ በዓለም ዙሪያ ባሉ የድርጅቱ ተቀጣሪዎች ባለቤትንት የተያዘ ነው።

እጅግ አስገራሚው ነገር ደግሞ ከአምስቱ የኩባንያው የቦርድ አባላት ሶስቱ አሜሪካዊያን መሆናቸው ነው።
ቲክቶክ በቻይና ውስጥ አገልግሎት የማይሰጥ ሲሆን የድርጅቱ መስሪያ ቤቶችም የሚገኙት በሲንጋፖርና በሎስ አንጀለስ መሆኑ ቢቢሲ በዘገባው ያትታል።

አሜሪካ፣ ኖርወይ፣ አውስትራሊያና የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት በመንግስት መስሪያቤት ንብረት በሆኑ ኮምፒውተሮችና ስልኮች ቲክቶክን መጠቀም ቀደም ሲል ሲከለክሉ ሶማልያ፣ ህንድ፣ ኢራን፣ ኪርጊስታንና ኔፓል ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ማገዳቸው ይታወሳል።