ወንጀለኞችን ወደ ህግ ለማምጣት መንግስት ግዴታውን እየተወጣ ነው- አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን

የፌዴራል መንግስት ወንጀለኞችን ወደ ህግ በማምጣት፣ የሃገርን ሉኣላዊነት ለማስጠበቅ እና ሰላሟ የተጠበቀች ኢትዮጵንያን ለመፍጠር ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ገለጹ፡፡
አምባሳደሯ ከ”ዶቸ ዌለ ቱ ዘ ፖይንት” ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ከዚህ በፊት በመንግስት የቀረቡ የሰላም አማራጮችን መለስ ብሎ ማየት እንደሚያስፈልግ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ወንጀለኞችን አድኖ ለህግ የማቅረብ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የህወሓት ቡድን በትግራይ ህዝብ ስም ሲነግድና ለወንጀል መፈጸሚያ መሳሪያ አድርጎ ሲጠቀምበት ለበርካታ ዓመታት መቆየቱን አምባሳደሯ አስታውሰው፣ እየተካሄደ ያለው ህግን የማስከበር ተግባርም ጦርነት ሳይሆን መንግስት ያቀረበውን የይቅርታና የእርቀ ሰላም አማራጭ ባለመቀበል በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሙሉ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን በቀጠናውና በአፍሪካ አህጉር ሰላም እንዲሰፍን ሰፊ ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በውይይት ላይ የተሳተፉት አቶ አስፋወሰን አስራቴ በበኩላቸው፣ መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ማድረጉን እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲመጣ ሲሰሩ እንደነበርና በአንጻሩ ህወሓት ለውጡ እውን እንዳይሆን በርካታ የጥፋት ተግባራትን ሲፈጽም እንደነበርም አንስተዋል፡፡
ለዚህም ባለፉት ሁለት እና ከዛ በላይ አመታት በሀገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮችን በማቀድና በማስተባበር በቁሳቁስና በገንዘብ ሲደግፍ እንደቆየ አመላክተዋል፡፡
መንግስት የበዛ ትዕግስት እና ይቅርታን ለጁንታው ቡድን በመስጠታቸው ተቃውሞ የደረሰባቸው ቢሆንም፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያን የመበታተን እና የማፈራረስ አጀንዳ ይዘው በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡

(በሜሮን መስፍን)