ወንጀል እንዲፈጸም ሰዎችን ማነሳሳት

#ሕግ_ይዳኘኝ

ወንጀል በአንድ ሰው የወንጀል ሃሳብ ጠንሳሽነት ተጀምሮ በዚሁ ሰው ድርጊት ፍፃሜውን የሚያገኝ ብቻ ሳይሆን ወንጀሉ እንዲፈጸም የሚያነሳሱ ሰዎችም ይሳተፉበታል።

ለወንጀል ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ከሚችሉ ተሳታፊዎች መካከል አነሳሽ አካላት ይገኙበታል።

በወንጀሉ በቀጥታ ተካፋይ የሆኑ ግለሰቦች ተገቢውን ቅጣት እንደሚቀበሉ የሚታወቅ ነው። ይሁን እንጂ ማንም ሰው ወንጀል እንዲፈጸም የተለያዩ ተሳትፎዎችን በማድረግ ያነሳሱ አካላትም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ወንጀል እንዲፈጸም ሰዎችን በማነሳሳት የተሳተፉ አካላት ሕጋዊ ቅጣታቸው እንዴት ይወሰናል የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ በዛሬው “ሕግ ይዳኘኝ” መርኃ ግብራችን እናስቃኛችኋለን።

በኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 36 መሰረት ማንም ሰው ወንጀል እንዲደረግ አነሳሳ የሚባለው አስቦ ሌላውን ሰው በመጎትጎት፣ ተስፋ በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ አንድ ወንጀል እንዲያደርግ ያግባባ እንደሆነ ነው፡፡

አነሳሹ የሚቀጣው ቢያንስ ወንጀሉ ተሞክሮ እንደሆነ ነው። የሚወሰንበትም ቅጣት ሊደረግ ለታሰበው ወንጀል ሕጉ በደነገገው ቅጣት ልክ ነው።

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለሌላው ሰው ወንጀል ለመፈፀም የሚያስችል ሐሳብ ስለሰጠ ብቻ አነሳሽ ነው ሊባል አይችልም። ስለሆነም አነሳሹ ፈፃሚውን ወንጀል እንዲፈፅም ቁርጠኛ ውሣኔ ላይ እንዲደረስ ካደረገው ብቻ አነሳስቷል ይባላል።

አነሳሹ ወንጀል ፈፃሚውን ባያነሳሳው ኖሮ ወንጀሉ አይፈጸምም ነበር የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው ለአነሳሹ ሕጋዊ ቅጣት የሚሰጠው። በአነሳሹ ተግባር እና በተነሳሹ የወንጀል ድርጊት መካከል በቂ የሆነ ግንኙነት ሊኖር ይገባዋል፡፡