ወደ ትግራይ በሳምንት 2 ጊዜ ይደረግ የነበረው የአየር በረራ በየቀኑ እንዲደረግ ተወሰነ

መጋቢት 20/2014 (ዋልታ) ወደ ትግራይ ክልል በሳምንት 2 ጊዜ ይደረግ የነበረው የአየር በረራ በየቀኑ እንዲደረግ ለተለያዩ ዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ ርዳታ አቅራቢ ተቋማት ሰቃድ ተሰጠ፡፡

የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱን ለማሳለጥና በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት መቆሙን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

ውሳኔው ከተወሰነበት ቀን አንስቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡

በሳምንት ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረውን የአየር በረራ በየቀኑ እንዲደረግ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ርዳታ አቅራቢ ተቋማት ፍቃድ ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት የመድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያዎች፣ ገንዘብና አልሚ ምግቦችን ረጂ ድርጅቶች በቻሉት መጠን በአየር ትራንስፖርት መጓጓዝ ጀምረዋል፡፡

ሌሎች በአየር ትራንስፖርት ሊጓጓዙ የሚችሉ የሰብአዊ ድጋፎችን እንዲያጓጓዙም የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ከዚህ አኳያ በረጂ ድርጅቶች አቅም ማነስ ወይም በራሳቸው አሠራር ሥርዓት የመዘግየት ሁኔታ ካልገጠመ በቀር በመንግሥት በኩል ፈጣን ርምጃ ተወስዷል፡፡

የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱን ተደራሽነት ለማስፋት በዓለም የምግብ ድርጅት በኩል 43 የከባድ መኪና ጭነት የርዳታ እህል በየብስ ትራንስፖርት በትግራይ ክልል የሰብአዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በአብኣላ መንገድ በኩል እንዲቀርብ ተፈቅዷል፡፡

በአሁኑ ሰዓት 20 የጭነት መኪናዎች የርዳታ እህሉን እንደጫኑ በአፋር ክልል በሠመራ ከተማ ቆመው ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ርዳታውን ለማቅረብ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባ ቢሆንም የሌላኛውን ወገን ቅን ትብብር ማግኘት አልቻለም፡፡ የዓለም የምግብ ድርጅት እንዲያጓጉዝ የተፈቀደው 43 የጭነት መኪና የርዳታ እህል ለተረጂዎች መድረስ አልቻለም። የዚህም ዋናው ምክንያት የአብኣላ የርዳታ ማቅረቢያ መንገድ በሕወሐት ታጣቂዎች በመዘጋቱ፣ርዳታው በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ ክልል ሊጓጓዝ አልቻለም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱን በተሟላ ሁኔታ ለማስኬድ ከተባባሪ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመሥራት ዛሬም ቁርጠኛ መሆኑን በድጋሚ ያሳውቃል፡፡ በመሆኑም የትግራይ ታጣቂዎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች ከመደርደርና የተዛቡ መረጃዎችን ከማሠራጨት ተቆጥበው የርዳታ እህሉ አቅርቦት እንዲሳለጥ የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡ መንግስት ያሳስባል፡፡

እንዲሁም የርደታ አቅርቦት ከሚተላለፍባቸውና በጉልበት ከያዙዋቸው የአፋርና የአማራ ክልል ወረዳዎች በመውጣት ግጭት ለማቆም የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ የዓለም አቀፍ ተቋማት በትግራይ ታጣቂዎች ላይ ጫና እንዲያደርግ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የትኛውንም አማራጭ በመጠቀም የርዳታ አቅርቦቱ እንዲሳለጥና ዜጎች በተረጋጋ ሁኔታ ኑሮአቸውን እንዲመሩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ቀና ተባባሪ ይሆናሉ ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡