ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ መረጃዎችን መጋራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

መጋቢት 20/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ‘ዲጂታል’ የሆነ የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ሥርዓትን በትብብር ለመምራትና መረጃዎችን መጋራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ እና የጅቡቲ የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ሀሰን ሀውመድ ተፈራርመዋል።
ተቋማቱ የሚጋሩት መረጃዎች በ’ጅቡቲ ወደብ ማኅበረሰብ ሥርዓት’ እና በኢትዮጵያ ‘የተቀናጀ የትራንስፖርት አስተዳደር ሥርዓት’ የተሰበሰቡ ናቸው ተብሏል።
ስምምነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ሥርዓትን በማቀናጀት ዘርፉን በትብብር ማዕቀፍ ለመመስረት እንደሆነም ተገልጿል።
መረጃዎቹ ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ እና በህጋዊ አካሄዶች እንደሚከወኑም ታውቋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የጭነት ትራንስፖርት ሥርዓታቸውን ለማሳለጥ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ስምምነቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን ኋላቀር የመረጃ አያያዝ በማዘመን ዘርፉን ለማሳደግ ይረዳልም ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ኃላፊነቱን ወስዶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በጅቡቲ በኩል ስምምነቱን አስመልክቶ የጅቡቲ ወደቦች እና ነጻ ዞኖች ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቡበከር ኦማር በበኩላቸው የትስስር ሥርዓቱ ለካርጎ ባለቤቶች ግልጽነትን የሚፈጥር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም የነበረውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በማሻሻል የአገልግሎት አሰጣጥ ፍሰትንም ያፋጥናል ሲሉ አክለዋል።