ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ነሐሴ 9/2015 (አዲስ ዋልታ) ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡

ስምምነቱ የክልሉን እምቅ ሀብቶች፣ ቱባ ባህሎችና የተፈጥሮ በረከቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አዲስ ዋልታ በሚታወቅበት የዘጋቢ ፊልሞቹ የክልሉን ብዙኃነት የሚያሳይና የተፈጥሮ ትሩፋቶችን የሚያጎላ የልማት ሥራዎችን በአብነት የሚቃኝ እንዲሁም የክልሉን ሰዋዊ እና ተፈጥሯዊ አቅሞች የሚያስተዋውቅ የአጋርነት ሥራ ለመስራት በመስማማታቸው ክልሉ ደስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ብሮድካስት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዘላለም እንዳሻው ተቋሙ የክልሉን ሁለንተናዊ ገፅታዎችን በማስተዋወቅ የስልጠና፣ ልምድ ልውውጥ፣ ፖሊሲ ጥናት እና አስፈላጊ ሙያዊ ድጋፎችን በማድረግ ከክልሉ ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ኃላፊ የሺዋስ ዓለሙ አዲስ ዋልታ ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ አጋዥ ሥራዎችን እየሰራ መቆየቱን አስታውሰው ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት በክልሉ ቅርንጫፍ ቢሮ ከፍቶ መስራት የሚችልበት መንገድ ለማመቻቸት ክልሉ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት የሽያጭ እና ደንበኞች አገልግሎት ንዑስ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ሙህዲን በከር በበኩላቸው ኮርፖሬቱ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመክፈት ፈጣን መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የዛሬውም ስምምነት የዚሁ ዕቅድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት እና ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት የክልሉ መንግስት የራሱን ሚዲያ የማቋቋም ዕቅድን በጥናት ላይ በተመሠረተ መንገድ በጋራ ለመስራት በስምምነት ፊርማ አረጋግጠዋል።

አክሊሉ ሲራጅ (ከቦንጋ)