ኮርፖሬሽኑ የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ የማጓጓዝ ሥራ መጠናቀቁን አስታወቀ

ነሐሴ 11/2015 (አዲስ ዋልታ) ለ2015/16 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ የማጓጓዙ ሥራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለምርት ዘመኑ ከውጭ የገዛው እና የመጨረሻው 500 ሺሕ ኩንታል ዩሪያ በዛሬው ዕለት ጅቡቲ ወደብ መድረሱ ተገልጿል፡፡

በዚህም ለምርት ዘመኑ ከውጭ የተገዛው 13 ሚሊየን 975 ሺሕ 520 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተጓጉዞ መጠናቀቁ ተጠቁሟል፡፡

ወደብ ከደረሰው ማዳበሪያ ውስጥ 12 ሚሊየን 603 ሺሕ 895 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደር ዩኒየኖች እየተሰራጨ ነው ተብሏል።

ወደብ የተራገፈውን ቀሪ ማዳበሪያ በጭነት ተሽከርካሪዎችና በባቡር ፉርጎዎች ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዙ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉም ተመላክቷል፡፡

ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው ከውጭ የተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 2 ሚሊየን 788 ሺሕ 940 ኩንታል ኤን ፒ ኤስ፣ 5 ሚሊየን 686 ሺሕ 580 ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ቦሮን እና 5 ሚሊየን 500 ሺሕ ኩንታል ዩሪያ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡