ዓለም ዐቀፍ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ጥምረት ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሆስፒታል የመድኃኒት እና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ጥር 3/2014 (ዋልታ) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው “ዓለም ዐቀፍ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ጥምረት” ለሰሜን ምዕራብ ዕዝ ደረጃ 3 ሆስፒታል ግምታቸው ከ500 ሺሕ ብር በላይ የሆኑ መድኃኒቶች እና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን ያስረከቡት የጥምረቱ ተወካይ መምህር ኮከብ ገዳሙ መንግሥት ዲያስፖራው ወደ አገሩ በመምጣት ከሕዝቡ ጎን እንዲቆም ጥሪ ባቀረበው መሰረት መገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
የጥምረቱ ተወካዮች በተለያዩ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር በጦርነቱ የተጎዱ ቦታዎችን በመጎብኘት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎች ለኅብረተሰቡ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው በዛሬው ዕለት ለዕዙ ሆስፒታል የተደረገው ድጋፍም ለ2ኛ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲያስፖራዎች ተግባር ምክር ቤት ጊዜያዊ ሥራ አስፈፃሚ ሊቀመንበር አለማየሁ አበበ በበኩላቸው ያለ ዲያስፖራው ተሳትፎ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ተፈላጊውን ግብ እንደማይመቱ ገልፀው ይህንኑ ለማጠናከር ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ውጤታማ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የሆስፒታሉ ጠቅላላ አገልግሎት ሎጀስቲክስ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ሰብለ ሙሉጌታ የጥምረቱ አባላት ከዚህ በፊት “እንቁጣጣሽን ከሠራዊት ጋር” በሚል መርህ ከ200 ሺሕ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው ይህንኑ በጎ ተግባር በማጠናከር ላደረጉት ድጋፍ በሆስፒታሉና በታካሚው ስም ምስጋና ማቅረባቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመልክቷል።