“ዓላማችን ሪከርዳችንን መስበር ነው!” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድሐምሌ 9/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ ታሪክ የመቀየር ጉዳይ ነው እንዲሁም ለትውልድ የመትረፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ተግባራት ነጻ የሆነ ቀን የመረጥነው ይህ ቀን ሊያልፈው የሚገባ ኢትዮጵያዊ ስለሌለ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞን ስንመርጥ የሥራ መጀመሪያችንን ተፈጥሮን በመታደግ እንድንጀምር ነው ብለዋል።

ፉክክራችን ከራሳችን ጋር ነው። ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና መንደሮች ከአምናው የበለጠ በመትከል የየራሳቸውን ሪከርድ እንደሚሰብሩ እናምናለን። እያንዳንዳችንም የየራሳችንን ሪከርድ መስበር አለብን ሲሉ በመልዕክታቸው ገለጸዋል።

ችግር የራሱን ሪከርድ እንዲሰብር ልንፈቅድለት አይገባም። ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው። ችግርን የምናሸንፈው መጀመሪያ የራሳችንን ፣ ቀጥሎ የአካባቢያችንን፤ በመጨረሻም የዓለምን ሪከርድ ስንሰብር ነው ብለዋል።

“እኔ ነገ በተደጋጋሚ ለመትከል ተዘጋጅቻለሁ። እናንተስ?” ሲሉ ዜጎች የአረንጓደ አሻራ ለማኖር ትኩረት እንደሰጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

“ነገ ሐምሌ 10 ቀን 2015 የራሳችሁን ሪከርድ በብዙ መጠን እስክትሰባብሩ ድረስ ዛፎችን ለመትከል ተዘጋጁ።” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡