ሰኔ 24/2014 (ዋልታ) የሀረማያ ዩኒቨርስቲ 17 ሚሊየን ብር የሚገመት ምርጥ ዘር በምስራቅ ሀረርጌ ለሚገኙ 20 ወረዳዎች ድጋፍ አደረገ።
ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ያደረገው አካባቢ የምርታማነት እጥረት ላጋጠማቸው በ20 ወረዳዎች ላይ ለሚገኙ ከ34 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች ነው።
በሀረማያ ዩኒቨርስቲ የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተስፋዬ ለማ እንዳሉት ዩኒቨርስቲው በአካባቢው በዝናብ እጥረት ምክንያት የምርታማነት እጥረት ላጋጠማቸው አርሶ አደሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት የሚችሉ ምርጥ ዘሮችን ድጋፍ አድርጓል።
የተደረገው ድጋፍም 17 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት 3 ሺሕ 416 ኩንታል መሆኑን አብራርተዋል።
የተደረገው የምርጥ ዘር ድጋፍም የስንዴ፣ የሽምብራ፣ የበቆሎና የበሎቄና ሌሎች ምርጥ ዘሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲ በቀጣይም ለአካባቢው አርሶ አደር ምርታማነት ለማጎልበት እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌታሁን ንጋቱ በዞኑ በበልግ ወራት 65 ሺሕ ሄክታር ለመሸፈን ታቅዶ 58 ሄክታር በዘር መሸፈን የተቻለ ቢሆንም የዝናብ መዘግየት ምክንያት በዘር ከተሸፈነው መካከል 92 በመቶ አለመብቀሉን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍም ችግሩን ከማቃለል አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
በእለቱ የተደረገው የምርጥ ዘር ድጋፍም በዞንና በወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ለአርሶ አደሩ እንደሚከፋፈል ተገልጿል።
የተደረገው ምርጥ ዘርም 5 ሺሕ 663 ሄክታር መሬት እንደሚሸፍን የተገለፀ ሲሆን ከ160 ሺሕ በላይ ምርት እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረማያ)