በትግራይ ክልል ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በፌዴሬሽን ምክር ቤት የዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ የህገ-መንግስት አስተምህሮና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥና ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ የህገ-መንግስት አስተምህሮና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ድጋፎችን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ በመሬት የወሰን ጉዳይ ላይ ህግና ስርአትን ተከትሎ ህዝብን መሰረት በማድረግ በአስቸኳይ ምላሽ በሚያገኝበት ዙሪያም መክሯል።
አሁን ባለው ወቅታዊ ችግር ምክንያትም ክልሉ አስፈላጊውን ገቢ ለማግኘት አዳጋች በመሆኑም ችግሩን በማየት የክልሉን በጀት በልዩ ሁኔታ መመደብ በሚቻልበት ሁኔታም ተወያይቷል።
በክልሉ ፀጥታና ደህንነት ጉዳይ እንዲሁም ተፈናቃዮችን አስፈላጊው ሂደት ተሟልቶ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚሰራም ከቋሚ ኮሚቴው ጋር በተደረገው ውይይት አቅጣጫ ተቀምጧል።
በተመሳሳይ ዜና ዋና ስራ አስፈጻሚው የአክሱምና የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ስራ ማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ፤ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አመራሮች ጋር መወያየታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በተለይም የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያ በቅርቡ ወደ ስራ እንዲመለስ እንደሚደረግ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን፣ የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ደግሞ አስፈላጊው የጥገና ስራ እንደሚከናወንለት ተመላክቷል።