የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ልዑክ ወደ ትግራይ ክልል አቀና

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና መማክርትን ያካተተ ልዑክ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመወያየትና ድጋፍ ለማድረግ ወደ ትግራይ ክልል ማቅናቱን የጉባኤው ዋና ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርትን ያካተተ ልዑክ ወደ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ማቅናቱ ነው የተጠቀሰው።

ልዑኩ በሚኖረው ቆይታ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚወያይም ነው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ልዑኩ በሚኖረው ቆይታ በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችንና፣

በተለይም በቤተ እምነቶች ላይ በደረሰው ጉዳት ዙሪያ እንደሚመክር ተናግረዋል።

በተጨማሪም ልዑኩ በቀጣይ ምን መሠራት እንዳለበት ከአከባቢው የእምነት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ከመንግሥት እና ከጸጥታ አካላት ጋር ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

የጉባኤው አባል የሆኑት የሐይማኖት ተቋማትም የድጋፍ ስራዎችን እንደሚያከናውኑና በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አገረ ስብከቶችን የሚመሩ ሊቃነ ጳጳሳት በኦን ላይን ያሰባሰቡት ድጋፍም ለህበረተሰቡ እንደሚለገስ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል።

(ምንጭ፡- ኢዜአ)