የህወሓት ቡድን ከአገራዊ ለውጡ በፊትና በኋላ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ህገ-ወጥ ተግባራትን ፈፅሟል- አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ

የህወሓት ቡድን ከአገራዊ ለውጡ በፊትና በኋላም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ የተለያዩ ህገ-ወጥ ተግባራት መፈፀሙን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።

አፈ ጉባኤው ዛሬ በሰጡት መግለጫ በትግራይ ክልል የተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን ተከትሎ በብቃትና በውጤታማነት መፈጸሙን ገልጸዋል።

ቡድኑ ህገ -ወጥ ድርጊቱን እንዲያቆም በምክር ቤቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግለትም ህገ-መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ከማድረግ ሊቆጠብ አልቻለም ነበር ብለዋል።

ይህን ተከትሎ የህወሓት ምክር ቤት እንዲፈርስ ስራ አስፈጻሚው አካልም ዕውቅና እንዳይኖረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወሱት አቶ አደም፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ምክር ቤቱ መወሰኑና ውሳኔውም ህገ-መንግስቱን ለማስፈጸም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 359/95 መሰረት በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ይህን ቡድን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የወሰደው እርምጃ የንጹሃን ዜጎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የህግ ማስከበር ዘመቻው በህገ-መንግስቱ መሰረት በብቃትና በውጤታማነት መፈጸሙንም ምክር ቤቱ ገምግሟል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በቀጣይም በትግራይ ክልል የሚከናወኑ ተግባራት በህገ-መንግስቱ መሰረት መፈጸም አለመፈጸማቸውን የሚከታተል መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በክልሉ ስላለው ሁኔታ በቀጣይ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባሉም ብለዋል።

በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ አካል የነበሩት ስልጣንና ተግባር የሚኖሩት በመሆኑ የክልሉን እቅድና በጀት ያጸድቃል ነው ያሉት።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በይፋ ስራውን መጀመሩን ተከትሎ በከተሞችና ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሚያሳትፍ መልኩ አመራሮችን መመደቡ ጥሩ ጅምር መሆኑንም አፈ ጉባኤ አቶ አደም መግለፃቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡