ሚያዝያ 19/2013 (ዋልታ) – ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያሉ ልዩነቶች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ይፈታሉ የሚል ጠንካራ እምነት እንዳላት ሱዳን ገለፀች።
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ውጤታማ እና ፈጣን መፍትሄ ላይ እንደሚደረስ እምነቷ መሆኑንም ሱዳን አስታውቃለች።
ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መሪ ሐሳብ የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት ነው ሱዳን የገለፀችው።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ህብረት እየተጫወተ ያለውን አስፈላጊ እና ፈር ቀዳጅ ሚና በማድነቅ በህዳሴው ግድብ ሙሌት እና አፈጻጸም ሂደቶች ዙሪያ ሶሰቱንም ሀገራት ያማከለ መፍትሄ እንደሚኖር እምነት እንዳለው የሱዳን የዜና ወኪል (SUNA) ዘግቧል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ሱዳን አቋሟን ለማስረዳት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የሚመራ ልዑክ ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ እንደምትልክ ገልጻለች።