ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል ስራ አስጀመረ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – ኢትዮ ቴሌኮም የኢንፎርሜሽን ቴከኖሎጂ እና የኔትወርክ መሰረተ ልማትን የሚያፋጥን ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል ስራ አስጀምሯል።

ማዕከሉ በከፍተኛ ደረጃ የሃይል ፍጆታን የሚቀንስ፣ በቀላሉ ፍላጎትን ተከትሎ ሊስፋፋ የሚችል እና ፈጣን የሲስተም ተከላ ለማድረግ የሚያስችለው እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ማእከሉን መርቀው በይፋ ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር “እየጨመረ ያለውን የግልና የመንግስት ተቋማት የመረጃ ክምችትና ስርጭት ጥራቱን የጠበቀ የመረጃ ማእከል መገንባት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ይህንን ፍላጎት ማስተናገድ እንዳልተቻለ አስታውሰው፤ ማዕከሉን መገንባት እንዳስፈለገ ጠቅሰዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹን መሰረት አድርጎ ማዕከሉን እንደገነባም ጠቁመዋል።

ማእከሉ ኩባንያው ለሚሰጠው ለሁሉም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኔትወርክ መሰረተ ልማቶች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኩባንያው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆኑ እንዲሁም የሀይልና ፍጆታው ያነሰና ለጥገና የሚወጣውን ወጪ 35 በመቶ እንደሚቀንስም ገልጸዋል።

በቅርቡ የተዋወቀው ‘ቴሌብር’ የተሰኘው አገልግሎትም በዚሁ ማእከል ምክንያት ለስራ ይበቃል ብለዋል።

መሰል ማእከላት በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገነቡም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

ማእከሉ ለኩባንያው ትልቅ አቅም የሚፈጥር እና በቀጣይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የሚረዳ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ በነባሩ የመረጃ ማእከል ላይ ያሉ ደንበኞችም በዚህ ሲስተም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።

ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለት ወራት እንደፈጀና ለዚህም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት ኢዜአ ዘግቧል።

የሞጁላር መረጃ ማዕከል ክላውድ ሲስተምን ማጎልበት፣ ቨርቹዋል ማድረግ፣ የዳታ ማእከልን የአገልገሎት አሰጣጥ ብቃት ለማሳደግ እንዲሁም የመረጃ ማዕከላትን አሠራር ማዘመን፣ ፈጣንና ውጤታማነት ማሻሻል፣ የኃይል ፍጆታን መቀነስ ከአይነተኛ ጠቀሜታዎቹ መካከል ናቸው።