የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት ፍትሃዊ፣ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ

ቴድሮስ ምህረት

ጥቅምት 1/2016 (አዲስ ዋልታ) በማንኛውም ሀገር የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ፍትሃዊ፣ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች የማይተካ ሚና እንዳላቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴድሮስ ምህረት ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት የ2016 በጀት ዓመት የዳኝነት ስራን በአዲስ ተስፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴድሮስ ምህረት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ደህንነትና መረጋጋት እንዲኖር ብሎም ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲኖር ለማስቻል የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለውና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳቸውን እያሻሻሉ የህዝብ አመኔታን ለማትረፍ ይሰራሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለዜጎችም ቀልጣፋና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ለመስጠት የዓመቱ የዳኝነት ስራ በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት ለዳኝነት አገልግሎቱ መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ተግባራት መከወናቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የዳኝነት ስራው ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሁም ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን ለማድረግ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በመፈተሽ የዳኝነት አገልግሎቱን ለህበረተሰቡ ምቹና ተደራሽ ለማድረግም በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በባለፈው ዓመት የፍርድ አፈፃፀምና የመሳሰሉ ተግባራትን በውጤታማነት ማከናወን ተችሏልም ብለዋል።

የዳኝነት አሰራሩን ከተለመደው አካሄድ በመቀየርና ቴክኖሎጂን በላቀ ሁኔታ በመጠቀም ቀልጣፋና ጥራት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ምቹና ዘመናዊ ህንፃ ለማስገንባት ቅድመ ሁኔታ ተጠናቆ መሰረተ ድንጋይ በቅርቡ እንደምጣልና ይህም ምቹ የስራ አከባቢ ከመፍጠር ባሻገር ምቹ የፍርድ ቤቱ ተደራሽነትን ያሳድጋል ብለዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2015 ዓ.ም ከቀረቡ 213 ሺሕ 113 መዛግብት ውስጥ ለ184 ሺሕ 467 መዛግብቶች እልባት ማግኘታቸውም ተማልከቷል፡፡

በታምራት ደለሊ