የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ባለስልጣን የላዳ ታክሲዎችን በዘመናዊ መኪኖች ለመቀየር ከታክሲ ማህበሩ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ሰራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን መንግስቱ ማህበሩ የላዳ ታክሲዎችን በዘመናዊ መኪኖች እንዲቀይር መንግስት ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ከመፍቀድ ባሻገር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከቀረጥ ነጻ ማስገባት የተፈቀደላቸው ማህበራት የቀረጥ ነጻ ጊዜው ረጅም ጊዜ የሚቆይ ባለመሆኑ በጊዜው እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ዘመናዊ ታክሲዎችን ለመውሰድ በአምስት ባንኮች የጀመሩትን ቁጠባ እና የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከ13 ሺህ በላይ ላዳ ታክሲዎች የነበሩ ቢሆንም አሁን በብልሽት እና በእርጅና ምክንያት ከአምስት እስከ ስድስት ሺህ ብቻ ቀርተዋል ነው የተባለው፡፡
በከተማው 185 የላዳ ታክሲ ማህበራት ያሉ ሲሆን፣ 10 ሺህ 500 አባላትን ያቀፈ ነው ተብሏል፡፡
ህገ ወጥ የታክሲ አገልግሎት የሚሰሩ ባለታክሲዎች ወደ ማህበራት እንዲገቡ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ጠይቀዋል፡፡
(በአካሉ ጴጥሮስ)