የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበሩ 29 ሺህ ዜጎች ዘላቂ በሆኑ የሙያ መስኮች ሊሰማሩ ነው

መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበሩ ከ29 ሺህ በላይ ዜጎች ዘላቂ በሆኑ የሙያ መስኮች ላይ እንደሚሰማሩ ተገለጸ።

በአዲስ አበባ ከተማ ከስድስት ዓመት በፊት በተጠና ጥናት 766 ሺህ 800 ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።

የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት 415 ሺህ ሰዎችን በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳምነው ጌራወርቅ እንዳሉት፤ ከእነዚህ መካከል ሞዴል ሆነው የወጡ 29 ሺህ 410 ሰዎች ዘላቂ ገቢ እንዲኖራቸው ለማድረግና ህይወታቸውን ለማሻሻል በሚያስችል የስራ መስክ ይሰማራሉ።

“ግለሰቦቹ ራሳቸውን ለመለወጥ ከገቢያቸው 20 በመቶ በመቆጠብ ያሳዩትን ተነሳሽነት መሰረት በማድረግ ኤጀንሲው 500 ዶላር ክፍያ በመፈጸም በመረጡት የስራ መስክ በዘላቂነት ህይወታቸውን ለማሻሻል በሚያስችል የሙያ መስክ ያሰማራቸዋል” ብለዋል።

ከስራ መስኮቹ መካከል ንግድ፣ የከተማ ግብርና፣ ኮንስትራክሽን፣ የአገልግሎት፣ የማኑፋከቸሪንግና ሌሎችም እንደሚገኙበት ገልጸው፤ በሙያ መስኮቹ የሚሳተፉ ሰዎች በመረጡት የስራ መስክ ስልጠና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ወደ ስራ መስኮቹ ለመሰማራት ዝግጁ ከሆኑት መካከል አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች እንደገለጹት፤ በልማታዊ ሴፍቲኔት በመሳተፋቸው በኑሯችው ላይ ለውጥ አምጥተዋል።

የልማታዊ ሰፍቲኔት ፕሮግራሙ ከመንግስትና አጋር ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻል ዓላማ ያለው ነው።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ፕሮግራሙ መስራት የሚችሉትን በማህበራዊ ልማታዊ ሴፍትኔት በማቀፍ ወደ ስራ የሚያሰማራ ሲሆን የመስራት አቅም የሌላቸውን ደግሞ በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል።