“ሰላምና ደህንነት በምርጫ ወቅት” በተሰኘ ርዕስ የአዲስ ወግ ውይይት ተካሄደ

መጋቢት 21/2013 (ዋልታ) – በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በወር አንዴ የሚደረገው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ሰላም እና ደህንነት በምርጫ ወቅት በሚል ርዕስ ተካሂዷል፡፡
ውይይቱ የሰላማዊ ምርጫዎች መገለጫዎች ምንድናቸው፡ ሰላምን የሚያንፀባርቅ ሀገር በቀል እና ዘመናዊ ተቋማትን መፍጠር እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃ በሰላማዊ ምርጫ ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተከፋፍሎ በሶስት ፕሮግራሞች የሚደረግ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በመጀመሪያው መርሀ ግብር በተደረገ ውይይት የሰላማዊ ምርጫ መገለጫዎች ምንነት ላይ በማተኮር ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ በርካታ ምሁራን ታድመውበታል፡፡
በመጪው ግንቦት ወር መገባደጃ እና ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የሚደረገው 6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምን መደረግ አለበት ሰላማዊ ምርጫስ መገለጫዎቹ ምንድናቸው በሚል ሀሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥነው የዛሬው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ የሴቶች ማረፊያ እና ልማት ዳይሬክተር በሆኑት ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር ንግግር ነበር የተጀመረው፡፡
ግድባችንን በጋራና በህብረት እየሰራን ለውጤት እንዳበቃነው ሁሉ ይህንንም ምርጫ ሁሉም በአንድነት በመቆም በሰላም እንዲጠናቀቅ ሊታገል ይገባል ብለዋል፡፡
ምርጫ ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ አውድን የሚጠይቅ በመሆኑ ሰላማዊ ምርጫን ለማካሄድ የዲሞክራሲ ስርዓት እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር ሊረጋገጥ ይገባል ያሉት በውይይቱ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የህግ ባለሙያው ዶ/ር መሰንበት አሰፋ ሰላማዊ ምርጫን ለማድረግ ሊደረጉ ይገባቸዋል ያሉትን ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ሌላኛዋ በውይይቱ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረበችው ወ/ሮ ህይወት አለማየሁ የስነ-ተግባቦት ተመራማሪ እና ባለሙያ በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ ቀደምት ምርጫዎች አሁን ለሚደረገው ምርጫ እድሎችን ያጠበበ የተከማቸ እዳን ያስቀመጠ በመሆኑ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥን ጨምሮ በርካታ ተግባራት ሊከናወኑ ይገባል ሲሉ ባቀረቡት ፅሁፍ ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምርጫ ቦርድ ከፀጥታው አካላት ጋር እና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ መስራት በሚችልባቸው መንገዶች ዙሪያም ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይቱ ተሳታፊዎችም በርካታ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
እንደ ማህበረሰብ ባለፉት ምርጫዎች ተከስተው የነበሩ የፀጥታ መደፍረሶች ሰዎች በምርጫው ንቁ ተሳታፊ እንዳይሆኑ የስነልቦና ጫናን የፈጠሩ በመሆኑ ይህን ለማስወገድ የዲሞክራሲ ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ተአማኒነት እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም በውይይቱ ተሳታፊዎች በስፋት ተነስቷል፡፡
በውይይቱ ታድመው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፣ ከየትኛውም ምርጫ በተለየ መልኩ ፍፁም ሰላማዊ እና ታአማኒነት ያለው ምርጫ ለማድረግ እየተሰራ በመሆኑ ይህንን ምርጫ ከ97ቱ አልያም ከሌሎቹ ምርጫዎች ጋር ማነፃፀር አያስፈልግም ምክኒያቱም በዚህ ምርጫ ኮሮጆ መስረቅም ሆነ ዜጎች የማይፈልጉትን እንዲመርጡ የማስገደድ ስራ የለም እና ሁሉም ማንን ለምን እንደሚመርጥ አውቆ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ምርጫው ላይ ሊሳተፍ ይገባልም ብለዋል፡፡
ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላሙን መጠበቅ አለበት ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
(በድልአብ ለማ)