የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ጊዜያዊ ውጤት ለህዝብ ይፋ ተደረገ

ጥር 30/2015 (ዋልታ) በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደው የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ጊዜያዊ ውጤት ለህዝብ ይፋ መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ውሳኔ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና አስተባባሪ መቅደስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት የድምፅ ቆጠራው ትናንት ማታ ተጠናቋል።

ጊዜያዊ ውጤቱም የድምጽ አሰጣጥ በተካሄደባቸው በ31 ማዕከላት ሥር በሚገኙ 3 ሺሕ 771 ምርጫ ጣቢያዎች ዛሬ ጠዋት ለህዝብ ይፋ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ህዝብ ውሳኔ በክልሉ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ትናንት መካሄዱን አስታውሰዋል።

በየደረጃው የተሰማሩ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎችና የጸጥታ አካላት የምርጫውን ሥነ ሥርዓት ለማስፈጸም በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀሳቸውንም ገልጸዋል።