ባንኩ በትግራይ ክልል የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ጥር 30/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የባንክ አገልግሎት በዛሬው እለት ድጋሚ አስጀመረ፡፡

ባንኩ ከብሄራዊ ባንክ ለክልሉ የተላከውን ብር ለቅርጫፎች በማከፋፈል በመቐለ ከተማ በሚገኙት ሁሉም ቅርንጫፎች እንዲሁም በዓብይ ዓዲ፣ ማይ ለሚን፣ ሳምረ፣ ግጀት፣ ሃይቂ መስሓል፣ ወርቅ አምባ፣ አፅቢ እና አጉላዕ በሚገኙ በአጠቃላይ በ31 ቅርንጫፎች የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በተጨማሪም በዓዲግራት፣ ውቕሮ፣ ፍረወይኒ፣ ሓውዜን፣ ዓዲጉዶም፣ ሒዋነ፣ ዓዲሽሁ፣ መኾኒ፣ ማይጨውና አካባቢው በሚገኙ ቅርንጫፎች በቅርብ ሰዓታት ውስጥ ባንኩ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ሥራ የጀመረባቸው አካባቢዎች የቴሌ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የተሟላባቸው ሲሆን የተወሰኑ የቴሌ መሰረተ ልማት ጥገና ባልተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች በቅርቡ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውሳኔን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ 5 ቢሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ወደ መቀሌ መላክ መጀመሩ ይታወቃል።

ይህ ጥሬ ገንዘብ ከትናንት ጀምሮ ለባንኮች መሠራጨት እንደሚጀምር ነው በወቅቱ የተገለጸው።