የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ አዋጅን አጸደቀ

ግንቦት 17/2015 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1294/2015 በአብላጫ ደምፅ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስበሰባ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ በሚመለከት ሰፊ ውይይት አድርጓል።

የሰው ሀብት ልማት የሥራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) አዋጁን ለማፅደቅ የቀረቡ የውሳኔ ሀሳቦችን አቅርበዋል።

ረቂቅ አዋጁ ለሀገር ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና በምርምር የላቀ እውቀት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የሚሰሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ዩኒቨርሲቲዎቹ ሙያዊ ተልዕኳቸውን በላቀ ብቃትና በነጻነት የሚተገብሩ ተመራማሪዎችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የጥናትና ምርምር፣ የትምህርትና የማህበረሰባዊ ነጻ አገልግሎት የሚያከናውኑበትን የፋይናንስ ምንጭ መሰብሰብና ሀገራዊ ልማትን ማገዝ የሚችሉበትን ነጻ ምህዳር ለመፍጠር ትልቅ ዕገዛ እንዲኖረው ተደርጎ በውይይት ዳብሮ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በክፍያ የሚያስተምሩ ከሆኑ መክፈል የማይችሉ ተማሪዎችን ያገለሉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት በምክር ቤት አባላት ተነስቷል።

መክፈል ለማይችሉ ድጎማ የሚደረግ ከሆነም ከፍለው በሚማሩና መክፈል በማይችሉ ተማሪዎች መካከል የማህበራዊ መደብ ልዩነት በመፍጠር በትምህርት ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል ሀሳብንም አንስተዋል።

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከሆኑ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ልዩነት እንደሌላቸው በማንሳት “የሀብታሞች ዩኒቨርሲቲ” ሊሆኑ ይችላል የሚል ስጋት አለን ብለዋል።

አብዛኛው የገጠር ተማሪዎችና በክፍያ ለመማር የሚያስችል በቂ ኢኮኖሚያዊ አቅም የሌላቸውን አብዛኛውን ተማሪዎች ያገለሉ የትምህርት ተቋማት እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባም አንስተዋል።

አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታ አኳያ ወቅታዊነቱ ላይ ጥያቄ ያነሱ የምክር ቤት አባላት የሊበራሊዝም አስተሳሰብ የተጫነው ነው ብለዋል።

ዩኒቨሲቲዎቹ ከዚህ ቀደም የገንዘብ አጠቃቀም ጉድለት በየዓመቱ በኦዲት እንደሚገኝባቸው መረጋገጡን በማስታወስ የአሁኑ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ አዋጅ የበለጠ ነፃነት ሰጥቷቸው ችግሩን ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት አንስተዋል።

የግዥ እና የኦዲት ስርዓታቸው በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባም አንስተዋል።

አዋጁ በመንግስት ግፊት ሳይሆን በዩኒቨርሲቲዎች የረጅም ጊዜ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ መዘጋጀቱን ያነሱም የምክር ቤት አባላት አሉ።

የዩኒቨርሲቲ መምህራን በስራቸው ልክ ተመዝነው እንዲቀጠሩና እንዲቀጥሉ መደረጉ ስንፍናን በማስወገድ ውጤታማ የትምህርት ሂደትን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

አዋጁ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ታሪክ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍትና ሚናውም የላቀ መሆኑን ከምክር ቤት አባላት ተነስቷል።

በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሀገር ዕድገት፣ በማህበረሰብ ለውጥ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ይህንን ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎች ገንዘብ ስብሰባ ላይ ብቻ እንዳያተኩሩ በአግባቡ መቆጣጠር የሚስችሉ ዝርዝር ደንቦችና መመሪያዎችን ማውጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ መንግስት ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ከተደራሽነትና ከጥራት አኳያ ከፍተኛ ለውጦችን እያካሄደ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የማድረግ ሀሳብም በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ስራን ወደ ከፍተኛ ስራ ያሸጋግራል ተብሎ ታምኖበታል ነው ያሉት።

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት የአሰራር ማሻሻያና ነጻነትን መቀዳጀት እንደሚገባ ሲጠይቁ በመቆየታቸው አዋጁ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አዋጅ መንግስት በተቀየረ ቁጥር የማይቀያየሩ ነጻና ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማሰብ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

መንግስት የዩኒቨርሲቲዎችን ተቋማዊ ነጻነት ለማረጋገጥ አዋጅ ሲያወጣ የመንግስትን የድጎማ በጀት ለማቋረጥ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም በአግባቡ በመጠቀም የቴክኖሎጂ ሽግግርና የምርምር ስራዎችን በተሻለ መንገድ እንዲያካሂዱ ለመፍቀድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ዓላማ የዩኒቨርሲቲዎችን ባህሪ ያላገናዘበ ምደባ፣ የዝውውርና የቅጥር ተግባራትን በመቀየር ብቃትና ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ አሰራረን ለመተግበር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ተቋማቱ የመንግስት መሆናቸውን ግንዛቤ መያዝ ይገባል ያሉት ተጠሪ ሚኒስትሩ በሀገር ደረጃ አካታችና የሁሉም ዜጎችን ተጠቃሚንት የሚያረጋግጡ፣ የተሻለ የመማር ማስተማር ጥራትን ያረጋገጡ ተቋማትን ለመገንባት አዋጁ መውጣቱን አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በምክር ቤት አባለት የተነሱ ስጋቶችን የሚመልስና ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ አዋጅ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የሚሆኑበት ዝርዝርና ጥብቅ መስፈርት መዘጋጀቱን፣ የትምህርት አተገባበራቸውም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል አካታች ያደረገ እንዲሆን መደንገጉን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ጠንካራ ኦዲት የሚደረግባቸው ሲሆን አስተዳደራዊ ሁኔታቸውን በብቃት ለመምራትም ብቁ የቦርድ አባላትና አመራር ለመሾም የሚያስችል ድንጋጌ በአዋጁ መካተቱን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1294/2015 በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ በአራት ተቃውሞ በ13 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቋን ኢዜአ ዘግቧል።