የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ

መስከረም 13/2013 (ዋልታ) – የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 100ኛ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የምክር ቤቱ ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

  1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የፌደራል የገቢ ግብር ደንብን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ከነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ የዋለ ሲሆን የኢትዮጵያ የገቢ ግብር ስርአት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተገቢው መንገድ መምራት የሚያስችል እንዲሆን በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡፣ሆኖም ጥቂት የደንቡ አንቀጾች ግልጽነት የሚጎድላቸውና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫናን ያሳደሩ ሆነው በመገኘታቸው ማሻሻያው አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ የማሻሻያ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
  2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ስለመንግስት አገልግሎት ጡረታ እና የግል ድርጅት ሰራተኞች ጡረታን ለመደንገግ በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡ መንግስት የዜጎችን ከአገሪቱ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ ሪፎርም እያካሄደ ከመሆኑም በላይ በዘርፉ በሚሰጡ አገልግሎቶች የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ይገኛል፡፡ በጡረታ አገልግሎት ዐቅድ ለሚሸፈኑ ባለመብቶች ፈጣን፣ ውጤታማና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታ ለማሳደግ እንዲሁም ግልጽ የፈንድ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት በስራ ላይ የነበሩትን አዋጆች ማሻሻል በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጆቹ ተዘጋጅተው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶች በማከል ይጸድቁ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
  3. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በቀረቡት ሰባት ከፍተኛ የማዕድን ልማት ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ባዋቀረው የህግ፣ የቴክኒክና የኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች ኮሚቴ የኢንቨስትመንቶቹ አዋጭነት፣ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ያላቸው ጠቀሜታ እና በኩባንያዎቹ መነሻ ካፒታል እንዲሁም ተአማኒነት በዝርዝር ተገምግሞ ስምምነቶቹ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንቶቹ መተግበር ከ4.7 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኙ፣ ከ1300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ፤ ኢንቨስትመንቶቹ በሚቋቋሙባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ የኮርፖሬት ሶሻል ሪስፖንሲቢሊቲ መርህ የሚያገለግሉ እና የአካባቢውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ ድንጋጌዎች በስምምነቶቹ መካተታቸውን በማረጋገጥ ጥቂት ግብዓቶችን በማከል ስምምነቶቹ እንዲፈረሙና ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል፡፡
  4. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የተሀድሶ ህክምና አገልግሎት ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የአገልግሎቱ ዋነኛ አላማ የተሀድሶ ህክምና መሳሪያዎችን በተለይም የሰው ሰራሽ አካላትን እና አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ማምረት እና አገልግሎቱንም በመላው አገሪቱ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በዘርፉ የልህቀት ማእከል በመሆን ማገልገል ነው፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ተወያይቶ የማሻሻያ ግብዓት በማከል የማቋቋሚያ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል፡፡