የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የልማት ስትራቴጂ እቅድ ለማዘጋጀት ውይይት እያደረገ ነው

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የቀጣይ 5 አመት ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂ እቅድ ለማዘጋጀት ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ  ቤቶች ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን መሰብሰብ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በቀጣይ 10 አመታት የብሔራዊ ስታቲስቲክ ስርዓቱ የሚመራበትን ፍኖተ-ካርታ እና ሶስተኛው ዙር የብሔራዊ ስታቲስቲክ ልማት ስትራቴጂ ሰነድ ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

የህዝብ እና ቤት ቆጠራ እንዲካሄድ እቅድ በመኖሩ ቅድመ ዝግጅትም ሲደረግ ነበር ያሉት አቶ ቢራቱ  በተለያዩ ምክንያቶች ለሶስት አመታት መራዘሙ በሌሎች የመረጃ አሰባሰቦች ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም እንዲኖር ማድረጉንም ጠቁመዋል።

በሌላ መልኩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝም የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ የራሱ ችግር እንደነበረው አንስተዋል።

የምክክር መድረኩ ለቀጣዮቹ 3 ቀናት የሚቆይ ሲሆን የአለም ባንክ ፤ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ስታቲስቲክስ ዲቪዥን ድጋፍ አድርገዋል ተብሏል።

(በደረሰ አማረ)