የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር ያስገነባውን ባለ 4 ወለል ህንፃ አስመረቀ

ሰኔ 03/2013 (ዋልታ) – በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር ያስገነባውን ባለ አራት ወለል ህንፃ አስመረቀ።

የህንፃው ግንባታ በ2011 ዓ.ም ሰኔ ወር የተጀመረ ሲሆን፣ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እና ጥራት በ72 ሚሊየን ብር መጪ ተገንብቶ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

ህንፃው ከ98 በላይ ክፍሎች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን፣ የዞኑ አስተዳደር ቢሮና የኦሮሚያ ብሮድካስት ሰርቪስን ጨምሮ የተለያዩ ቢሮዎችን ያጠቃልላል ነው የተባለው።

ዞኑ በተቀናጀ መልኩ ለነዋሪው አገልግሎት ለመስጠት ችግር የነበረበት እንደሆነና ይህም ህንፃ  ለችግሩ መፍትሄ የሚሰጥ ከመሆኑ በተጨማሪ ምቹ የስራ አከባቢ የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡

በምረቃ ሥነሥርዓት ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ ኢንቴን ጨምሮ የግምቢ ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

(በሚልኪያስ አዱኛ)