የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ገቢ እና ወጪ እቃዎች ስርቆት ለመከላከል ውይይት እየተካሄደ ነው

ሞጆ፣ የካቲት 06/2013 (ዋልታ) – የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ገቢ እና ወጪ እቃዎች ላይ እየደረሰ የያለውን የስርቆት ወንጀል ለመከላከል ከፍትህና ህግ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

ውይይቱ የማዕከሉ ግንባታ ሂደት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል በገቢ እና ወጪ እቃዎች ላይ እያጋጠመ ያለውን ስርቆት ለመግታት ያለመ ነው ተብሏል::

ከአካባቢው ማህበረሰብና ከፀጥታ አካላት ጋር ምክክር መደረጉ ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚያስችል እንደሆነ የኢትዮዽያ ማሪታይም ጉዳይ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ገልጸዋል::

የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል በገቢና ወጪ እቃዎች ላይ እያጋጠመ ያለው የስርቆት ወንጀል የማዕከሉን ግንባታ የሚያጓትትና ውጤታነቱን የሚያሰናክል መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ እና ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከፀጥታ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል::

ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቅንጅት በመስራት የመፍትሄ አካል እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል::

(በሄብሮን ዋልታው)