የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለተፈናቀሉ ወገኖች የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የካቲት 05/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በትግራይ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኮሚሽን በትግራይ እና ቤኒሻንጉል ክልል ለሚከናወን ሰብአዊ ድጋፍ የ81 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ቀርፆ እየሠራ መሆኑን ጠቅሶ፤ ከዚህ ውስጥ 35 ሚሊዮን 940 ሺህ ብር የፋይናንስ ድጋፍ ተገኝቶ ተግባራዊ ሥራ ተጀምሯል ብሏል።

የኢፕድ ዘገባ እንዳመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች በተከሰተው ወቅታዊ ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው እርዳታ እና ድጋፍ እንዲደረግ በወሰነው ውሳኔ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሥር በተከፈተው የባንክ ሒሳብ የአዲስ አበባ ሀገረ የስብከት 15 ሚሊዮን ብር እርዳታ ገቢ አድርጓል ሲልም ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡